2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3
Amharic NT

1እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? 2ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። 3እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው።

4በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። 5ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤ 6እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።

7ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ 8የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? 9የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። 10ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። 11ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና።

12እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን እጅግ ገልጠን እንናገራለን፥ 13የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም። 14ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። 15ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ 16ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። 17ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። 18እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

2 Corinthians 2
Top of Page
Top of Page