ወደ ሮሜ ሰዎች 7
Amharic NT

1ወንድሞች ሆይ፥ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን? 2ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች። 3ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም።

4እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፥ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ። 5በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበርና፤ 6አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም።

7እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ። አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። 8ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና። 9እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ 10ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ 11ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። 12ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት።

13እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር።

14ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። 15የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። 16የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። 17እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ። 18በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። 19የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። 20የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ።

21እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። 22በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ 23ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። 24እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? 25በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Romans 6
Top of Page
Top of Page