የዮሐንስ ወንጌል 17
Amharic NT

1ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው። 2 3እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። 4እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ 5አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።

6ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ 7ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤ 8የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። 9እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ 10የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ። 11ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። 12ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም።

13አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። 14እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። 15ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። 16እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። 17በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። 18ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ 19እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።

20ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። 21

22እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። 23 24አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።

25ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ 26እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

John 16
Top of Page
Top of Page