ወደ ፊልሞና 1
Amharic NT

1የክርስቶስ ኢየሱስ እስር ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥ 2ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነ ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን፤ 3ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

4በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 5 6የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ 7የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና።

8ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ 9ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ።

10አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። 11 12እርሱን እልከዋለሁ፤ 13አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ 14ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። 15ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ 16ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም።

17እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቈጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። 18በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤ 19እኔ ጳውሎስ። እኔ እመልሰዋለሁ ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አልልህም። 20አዎን፥ ወንድሜ ሆይ፥ በጌታ እኔ እንድጠቀምብህ ይሁን፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ።

21ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ።

22ደግሞ ከዚህም ጋር የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ፤ በጸሎታችሁ ለእናንተ እንድሰጥ ተስፋ አደርጋለሁና።

23በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኔ ጋር የታሰረ ኤጳፍራ 24አብረውኝም የሚሰሩ ማርቆስና አርስጥሮኮስ ዴማስም ሉቃስም ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

25የጌታችን የኢሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Titus 3
Top of Page
Top of Page