የማርቆስ ወንጌል 4
Amharic NT

1ደግሞም በባሕር ዳር ሊያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በታንኳ ገብቶ በባሕር ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕር ዳር በምድር ላይ ነበሩ። 2በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፥ በትምህርቱም አላቸው። ስሙ። 3እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። 4 5ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። 7ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። 8ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። 9የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ።

10ብቻውንም በሆነ ጊዜ፥ በዙሪያው የነበሩት ከአሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 11እንዲህም አላቸው። ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥ እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል። 12

13አላቸውም። ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? 14ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፥ 15በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። 16እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ 17ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። 18በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ 19የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። 20በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።

21እንዲህም አላቸው። መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? 22እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። 23የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። 24አላቸውም። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። 25ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።

26እርሱም አለ። በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ 27እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። 28ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። 29ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።

30እርሱም አለ። የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? 31እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥ 32የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።

33መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥ 34ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።

35በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ። ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው። 36ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 37ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። 38እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። 39ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። 40እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። 41እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Mark 3
Top of Page
Top of Page