የዮሐንስ ወንጌል 11
Amharic NT

1ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። 2ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። 3ስለዚህ እኅቶቹ ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል ብለው ወደ እርሱ ላኩ። 4ኢየሱስም ሰምቶ። ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ። 5ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። 6እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ 7ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ። ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው። 8ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት። 9ኢየሱስም መልሶ። ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ 10በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው። 11ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ። ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። 12እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። 13ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። 14እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ። አልዓዛር ሞተ፤ 15እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው። 16ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት። ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ።

17ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። 18ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። 19ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። 20ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። 21ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ 22አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው። 23ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት። 24ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው። 25ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ 26ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት። 27እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው።

28ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ። መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት። 29እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤

30ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። 31ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። 32ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው። 33ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ 34ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት። 35ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። 36ስለዚህ አይሁድ። እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ። 37ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ። ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ።

38ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። 39ኢየሱስ። ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው። 40ኢየሱስ። ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት። 41ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ። አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። 42ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ። 43ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ። አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። 44የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም። ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።

45ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ 46ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው።

47እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው። ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። 48እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ። 49በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ 50ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። 51ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ 52ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። 53እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።

54ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።

55የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በመቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው። ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን? ተባባሉ። 57የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቀው ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው አዘው ነበር።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

John 10
Top of Page
Top of Page