Amharic NT 1እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። 2አላቸውም። ስትጸልዩ እንዲህ በሉ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ 3የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ 4ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን። 5እንዲህም አላቸው። ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ። ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥ 6አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? 7ያም ከውስጥ መልሶ። አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? 8እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። 9እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። 10የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። 11አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? 12ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? 13እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው? 14ዲዳውንም ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ ሕዝቡም ተደነቁ፤ 15ነገር ግን ከእነርሱ አንዳንዱ። በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። 16ሌሎችም ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። 17እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። 18እኔ አጋንንትን በብዔል ዜቡል እንዳወጣ ትላላችሁና ሰይጣን ደግሞ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? 19እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። 20እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። 21ኃይለኛ ሰው ጋሻና ጦር ይዞ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ገንዘቡ በሰላም ይሆናል፤ 22ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ መጥቶ ሲያሸንፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን ጋሻና ጦር ይወስድበታል ምርኮውንም ያካፍላል። 23ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። 24ርኵስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባያገኝም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ 25ሲመጣም ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል። 26ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሌሎችን ሰባት አጋንንት ከእርሱ ጋር ይይዛል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። 27ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ። የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። 28እርሱ ግን። አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ። 29ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር። ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። 30ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። 31ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። 32የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 33መብራትንም አብርቶ በስውር ወይም በእንቅብ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። 34የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል። 35እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተመልከት። 36እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ የጨለማ ቍራጭ የሌለበት ብሩህ ቢሆን፥ መብራት በደመቀ ብርሃን እንደሚያበራልህ በጭራሽ ብሩህ ይሆናል። 37ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ። 38ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ። 39ጌታም እንዲህ አለው። አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል 40እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? 41ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። 42ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር። 43እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ። 44እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። 45ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ማለትህ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው አለው። 46እርሱም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ ሕግ አዋቂዎች፥ አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፥ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፥ ወዮላችሁ። 47አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ። 48እንግዲህ ለአባቶቻችሁ ሥራ ትመሰክራላችሁ ትስማማላችሁም፤ እነርሱ ገድለዋቸዋልና፥ እናንተም መቃብራቸውን ትሠራላችሁ። 49ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል፥ 50ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፥ 51ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል። 52እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ። 53ይህንም ሲናገራቸው፥ ጻፎችና ፈሪሳውያን በአፉ የተናገረውን ሊነጥቁ ሲያደቡ፥ እጅግ ይቃወሙና ስለ ብዙ ነገር እንዲናገር ያነሣሡ ጀመር። 54 Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia! Bible Hub |