የሉቃስ ወንጌል 24
Amharic NT

1ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። 2ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ 3ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። 4እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ 5ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። 6የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ። 7 8ቃሎቹንም አሰቡ፥ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። 9 10ይህንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱም ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። 11ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። 12ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ።

13እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ 14ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። 15ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ 16ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። 17እርሱም። እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው። 18ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ። አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። 19እርሱም። ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ 20እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። 21እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። 22ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ 23ሥጋውንም ባጡ ጊዜ። ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። 24ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም።

25እርሱም። እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ 26ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። 27ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።

28ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው። 29እነርሱ። ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። 30ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ 31ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እርስ በርሳቸውም። በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ። 33በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም። ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። 34 35እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው።

36ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። 37ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። 38እርሱም። ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? 39እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። 40ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ። በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። 42እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ 43ተቀብሎም በፊታቸው በላ።

44እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። 45በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ 47በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። 48እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።

50እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። 52እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ 53ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Luke 23
Top of Page
Top of Page